Kidane Mihret Mehaber’s Poem

ለምናፈቅራት፣ ለምናከብራት፣ መስከረም 16 ዕለት ለተለየችን፣ ለ ወ/ ምርጥዓለም ታከለ፣ ከኪዳነ ምህረት የፅዋ ማህበር፣ እህቶችዋ የቀረበ የሀዘን መግለጫ።

ቃል ኪዳኗ ፅኑ ጊዜ ማይቀይረው፣

እምነቷ ጠንካራ፣ ህመም የማይጥሰው፡

የእህታችን ምክርዋ አንጅት የሚያርሰው፡

ልቧ ቂም የማይዝ ዞራ የማትወቅሰው፣

ምርጥዓለም ታከለ መልካም ሰው ድንቅ ሰው፡

መልክሽ ያማረ ነው ፀባይን ጨምሮ፡

ሞት ባንችም ጨከነ አዬ ጉድ ዘንድሮ።

አልፈለግንም መስማት ታማለች መባልን፣

ውዷ ሰብሳቢያችን ደጓ ምርጥዓለምን፡

ትድኛለሽ ብለን አይን አይንሽን ስናይ፣

ምነው ጨከንሺብን? የጓደኛ አታላይ።

ሲከፋን ተከፍተሽ ስናለቅስ አልቅሰሽ፣

ሁሉንም ትተሺው ምነው ጥለሽን ሄድሽ?

ተይ እንመካከር እንደልማዳችን፣

ከአሁኑ ናፈቅነው ለዛ ቁም ነገርሽን።

በጣም የከፋ ነው የወደቀው ሀዘን፣

ደጓ እህታችንን ክፉ ሞት ሲነጥቀን።

ታከብራት ነበረ ሳለች በህይወት፣

ልጇን ሰበሰበች ኪዳነ ምህረት።

ምርጥዮ፣ ምርጥዮ ምርጣለም እያሉ፡

ባገርም በውጪም በየቦታው ያሉ፡

ወገን ዘመዶቿ ሁሉም ይጣራሉ፡

ወደ አምላክ መሄዷን ያልተረዱ ሁሉ።

ተዋት ተኝታለች ትለናለች ሥርጉት

የቅርብ አስታማሚ የምርጣለም እህት።

ልዩወርቅ ፀሀይ የምሥራች ቆንጂት፡

ሶስናና አስቴር እንዲሁም ወይንሸት፡

የፅዋ አጣጮችዋ የኪዳነምህረት

አንስለችም ነበር ማስታመም በዕውነት

ምርጥ ጥላን ሄደች ሳንሰነባበት።

የዚች ዓለም ምሥጢር ጨርሶ አይወራ፣

ሁሉንም ስትወስድ እንደው በየተራ፡

ትንሽ ትልቅ ሳትል ማንንም ሳትፈራ፡

ምነው ተፈጠነ ምርጤ ያንችስ ተራ።

ሁላችን አንቀርም ካለሽበት ቦታ፡

ፁዋው ይደርሰናል ሁላችን በተርታ።

እንግዲህ ደህና ሁኚ ኩኩሻ እህታችን፡

እንሰናብትሽ በአንድነት ሁላችን

የኪዳነ ምህረት ማህበርተኛችን።

እስከምንገናኝ በሰማይ ቤታችን፡

የምንጽናናበት ይኼው ነው ተስፋችን።

ከእንግዲህ ይቅርብን ጨርሶ መዋተት

አምላክ ፈቅዷልና ሊያኖርሽ በገነት።

እዘኝልን ለኛ አንቺስ ጨርስሻል፡

ከመድሃኔዓለም፣ ከእመቤታችን ጋር መሆንን መርጠሻል፤

ያለሺው በገነት ከቅዱሳን ጋራ፡

እንከተላለን አንቀርም በተራ።